ምኞትን ለመዋጋት የሚጠቅሙ ስልቶች
Written by John Piper

ይህን ስጽፍ ወንዶችንም እና ሴቶችንም በማሰብ ነው። ለወንዶች በእርግጥ ግልጽ ነው። በወሲባዊ ምስሎች የሚመጣ ፈተናን ለማጥፋት የሚደረግ ውጊያ አስፈላጊ ነው። ለሴቶች ግን ላይስተዋል ይችላል። ይሁን እንጂ ለእውቅ ሰዎች እና ስለ ግንኙነቶች የሚኖርን ቅዠት አስፍተን ፈተናውን ብናስብ ልክ እንደ ወንዶች ሁሉ ለሴቶችም ታላቅ እንደሆነ ይታየናል። ምኞት ስል ወደ ብልሹ ወሲባዊ ምግባሮች የሚመሩ ሃሳቦች እና መሻቶችን ነው። ልክ ያልሆኑ መሻቶችን በመዋጋት ጊዜ የሚያገለግሉ ስልቶች እኚሁላችሁ።
ማስወገድ:- ልክ ያልሆነ መሻትን ሊቀሰቅሱባችሁ የሚችሉ እይታዎችን እና ሁኔታዎችን ሊሆን በሚችል እና በተቻላችሁ መጠን አስወግዱ። “ሊሆን በሚችል እና በተቻላችሁ መጠን” ያልኩበት ምክንያት አንዳንድ ለፈተና የሚያጋልጡ ነገሮችን ማስወገድ ስለማይቻል ነው። “ልክ ያልሆነ መሻት” ያልኩበት ምክንያት ደግሞ ስለ ወሲብ ፣ ምግብ እና ቤተሰብ ያሉን መሻቶች ሁሉ መጥፎ ስላልሆኑ ነው። የማይጠቅሙን እና ልክ ያልሆኑ ባሪያ ሊያደርጉን ሲጀምራቸው እናውቃቸዋለን። ድካማችንን እና ምን እንደሚያስነሳቸውም ደግሞ እናውቃለን። “ማስወገድ” መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስልት ነው። “ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል” (2 ጢሞቴዎስ 2፡22)። “ምኞቱንም እንዲፈጽም ለሥጋ አታስቡ” (ሮሜ 13፡14)።
እንቢ በሉ:- ለሚመጡባችሁ የምኞት ሃሳቦች ሁሉ በ 5 ሰከንዶች ውስጥ እንቢ በሉ። ይህንንም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሥልጣን አድርጉት። በኢየሱስ ስም እንቢ! በሉት። ከአምስት ሰከንድ የሚበልጥ ጊዜ የላችሁም። እሰቲ ሳትቃወሙት ከዚያ በላይ ጊዜ ስጡት። ልታነቃንቁት እስካትችሉ ድረስ በታላቅ ኃይል መጥቶ መኖር ይጀምራል። ካስፈለጋችሁ ድምጽ አውጥታችሁ በሉት። ጠንካራ እና እንደ ጦረኛ ሁኑ። ጆን ኦውን እንዳለው “ኃጢያትን ግደሉት አሊያም ኃጢያት እራሱ ይገድላችኋል”። በኃይል አጥቁ። “ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል” (ያዕቆብ 4፡7)።
ኃጢያትን ግደሉት አሊያም ኃጢያት እራሱ ይገድላችኋል
ጆን ኦውን

የክርስቶስጠባሳዎች
መልሱ:- ክርስቶስን የእርካታችሁ ጥግ በማድረግ ልባችሁን ወደ እርሱ መልሱ። እንቢ ማለት ብቻ በቂ አይሆንም። ከመከላከል ወደ ማጥቃት መሸጋገር አለባችሁ። እሾህን በእሾህ እንደሚባለው የኃጢያትን ተስፋዎች በክርስቶስ ተስፋዎች ተዋጓቸው። ኃጢያት ስለሚዋሸን መጽሐፍ ቅዱስ በ ኤፌሶን 4፡22 ላይ “የሚያታልል ምኞት” ይለዋል። ሊሰጡን ከሚችሉት በላይ ቃል ይገቡልናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ባለማወቃችሁ አስቀድሞ የኖራችሁበትን ምኞት” (1 ጴጥሮስ 1፡14) ይላቸዋል። ሞኞች ብቻ ናቸው እጅ የሚሰጡት። “እርሱ እንዲህ ስቶ ይከተላታል፥ በሬ ለመታረድ እንዲነዳ” (ምሳሌ 7፡22)። ማታለል የሚሸነፈው በእውነት ብቻ ነው። አለማወቅ የሚሸነፈው በአውቀት ነው። ይህ እውነት ታላቅ እና የሚያምር እውነት መሆን አለበት። ለዚህም ነው “Seeing and Savoring Jesus Christ” የሚለውን መጽሐፌን የጻፍሁት። ልባችንን ታላላቅ በሆኑ በኢየሱስ ተስፋዎች እና ደስታዎች ማስታጠቅ አለብን። “እንቢ!” እንዳልን ወዲያው ወደ እነዚህ መዞር አለብን።
መያዝ:- ሌሎችን ምስሎች እስኪያስወጣ ድረስ የክርስቶስን ተስፋዎች እና ደስታዎች አጥብቃችሁ በልባችሁ ያዙ። “ኢየሱስን ተመልከቱ” (ዕብራውያን 12፡2)። ብዙዎች የሚወድቁት አዚህ ጋር ነው። ወዲያው እጅ ይሰጣሉ። “ለማስወጣት ሞከርኩ ግን አልሆነልኝም” ይላሉ። ከዚያም እጠይቃቸዋለሁ “ምን ያህል ሞከራችሁ?” “ምን ያህል ልባችሁን ሰጣችሁት?” ልባችን እንደ ጡንቻ ነው። በኃይል ልንለጥጠው እንችላለን። መንግስተ ሰማያትን በኃይል ተናጠቋት (ማቴዎስ 11፡12)። ጨካኞች ልትሆኑ ያስፈልጋችኋል። የክርስቶስን ተስፋ በዓይኖቻችሁ ፊት አጥብቃችሁ ያዙ። ያዙት! እንዳትለቁት! እስከመቼ? አስፈላጊ ሆኖ እስከተገኘ ጊዜ ድረስ። ተፋለሙት! ስለክርስቶስ ስትሉ እስክታሸንፉት ድረስ ተፋለሙት! ልጃችሁ ላይ የሆነ ነገር ሊወድቅበት እና ሊጫነው ቢል በእርግጠኝነት በሙሉ አቅማችሁ ትይዙታላችሁ እርዳታም ትጠይቃላችሁ።
ተደሰቱ:- በሚበልጥ እርካታ ተደሰቱ። በክርስቶስ የመደሰት አቅማችሁን አሳድጉ። በብዙዎች ውስጥ ምኞት የሚነግሠው ለክርስቶስ ጥቂት ፍላጎት ስላላቸው ብቻ ነው። በክርስቶስ ያለን ደስታ ጥቂት ስለሆነ በቀላሉ ወደ መታለል እንገባለን። “ይሄ እኔ አይደለሁም” ብቻ አትበሉ። ለኢየሱስ ያላችሁን ፍቅር ለማነሳሳት ምን እርምጃ ወስዳችኋል? ለደስታችሁ ተፋልማችኋል? ለውጥ ሊመጣ አይችልም ብላችሁ ተስፋ አትቁረጡ። የተፈጠራችሁት ወሲብን አጥብቃቸችሁ ከያዛችሁት በላይ በሙሉ ልባችሁ ክርስቶስን እንድትወድዱት ነው። ለኢየሱስ ያላችሁ ፍላጎት ጥቂት ከሆነ ደስታዎችን ማወዳደር በላያችሁ ላይ ያይላል። ስለሌላችሁ እርካታ እግዚአብሔርን ለምኑት። “በማለዳ ምሕረትህን እንጠግባለን በዘመናችን ሁሉ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን” (መዝሙር 90፡14)። ከዚያም በዓለም ሁሉ ላይ እጅግ ድንቅ የሆነውን ጌታ ማንነት እስክታዩ ድረስ ፈልጉት።
ዘወር ማለት:- ከሚያጋልጧችሁ ባህርያት እና ምንም ካለማድረግ ዘወር ብላችሁ ወደሚጠቅም ሥራ ግቡ። ምኞት በመዝናኖት ጓሮ ውስጥ የበለጠ ቶሎ ያድጋል። ልትሰሩት የምትችሉትን መልካምን ሥራ ፈልጉና በሙሉ ኃይላችሁ አድርጉት። “ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ” (ሮሜ 12፡11) “የምትደላደሉ፥ የማትነቃነቁም፥ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ” (1 ቆሮንቶስ 15፡58)። በሥራ ተጠመዱ። ተነሱና ሌላ ነገርን ሥሩ። ክፍላችሁን ጥረጉ። የለቀቀ ምስማር ካለ አጥብቁ። ደብዳቤ ጻፉ። እናም ሁሉንም ስለ ኢየሱስ ስትሉ አድርጓቸው። የተፈጠራችሁት ለመፍጠር እና ለመቆጣጠር ነው። ክርስቶስ የሞተላችሁ “መልካሙንም ለማድረግ የምትቀኑ” (ቲቶ 2፡14) እንድትሆኑ ነው። የሚያታልልን ምኞት ለመልካም ሥራ ባለ ቅንዓት ቀይሩት።
“እጆቼን እና እግሮቼን ተመልከቱ፡እኔው ራሴ ነኝ ደግሞም ንኩኝ እና እዩ ይህንንም ብሎ እጆቹን እና እግሮቹን አሳያቸው” ሉቃ 24፡39
በዚህ የፋሲካ ወቅት አንድ ጥያቄ በአዕምሮዬ ይመላለሳል። ይህም ክርስቶስ በእጆቹ በእግሮቹ እና በጎኑም ያሉትን የዳኑ የቁስል ምልክቶች፣ ከሙታን ከተነሳ በኋላ በአካሉ ላይ እንዲኖሩ ለምን እንደመረጠ ነው። ከሙታን የተነሳው ይህ አዲስ ሰውነት በአምላክነት ክብሩ በዙፋኑም ላይ ይህን የአንድ ቀን ትዝታን ያዘለ ጠባሳ ሁሌ አብሮት እንዲኖር ለምንስ መረጠ?
ብዙዎቻችን በሰውነታችን ላይ ቢያንስ አንድ ጠባሳ አለን፤ ምናልባት በልጅነታችን የወደቅንበት፤ ከሰው ተጣልተን የተፈነከትንበ ወይም የቀዶ ጥገና ህክምና ያደረግንበት ሊሆን ይችላል።አብዛኛው እነዚህ ጠባሳዎች አካላችን ያለፈበት የህመም ጊዜ ትውስታዎች የመዳናችንም ምልክቶች ናቸው አልፎ አልፎ ደግሞ መልካም ሰዎች አሉ፤ ከራሳቸው ህመም አልፈው የሌላውን ሊሽከሙ የአካል ክፍላቸውን በመለገስ ጠባሳን በአካላቸው ላይ ያኖራሉ።
ክርስቶስ የእኛን ህመም ለመሽከም ሙሉ አካሉን ሰጠ። እኛን ለመዋጀት ሞትን የህይወቱ አላማ አድርጎ ወደ ምድር ወረደ፤ የቀጠረለትም ቀን ሲደርስ ጀርባውን ለግርፋት እጅ እና እግሩን በሚስማር ለመቸንከር፣ ለመስቀልም ግርፋት አሳልፎ ሰጠ።
“በእርግጥ እርሱ ደዌያችንን ወሰደ፤ ህመማችንንም ተሽከመ ስለ መተላለፋችንም ተዋጋ፣ ስለበደላችንም ደቀቀ” ኢሳ 3፡ 4-5
ታዲያ ክርስቶስ አምላክ ሆኖ ሳለ፣ አዲስም ሰውነት ለብሶ ሞትን ድል ሲነሳ ለምንስ በእጆቹ እና በእግሮቹ በጎኑም ያሉ ጠባሳዎች አብረውት እንዲቀሩ ወደደ? ይህ እኮ አምላክ በቀላሉ ሊያጠፋው የሚችለው ነገር አይደለምን? የመከራው የስቃዩንም ትዝታ ለብሶ ሊኖር ለምንስ አስፈለገው?
1. የክርስቶስ ጠባሳዎችለደቀ መዛሙርቱ ከሞት የመነሳቱ ማረጋገጫ ናቸው
“በዚያኑ እለት በሳምንቱ መጀመሪያ ቀን በምሽት ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን በመፍራት በሮችን ቆልፈው ተሰብስበው ሳለ ኢየሱስ መጣና በመካከላቸው ቆሞ ‘ሰላም ለእናንተ ይሁን’ አላቸው። ይህን ብሎ እጆቹን ጎኑን አሳያቸው።’ ዮሐ 20፡19-20
ኢየሱስ ከሰላምታ ባለፈ የእጆቹን እና የጎኑን ጠባሳ ለሐዋሪያቱ አንክሮት ሰጥቶ እንዳሳያቸው ይህ ክፍል ያሳየናል።
ኢየሱስ ለሐዋሪያቱ በተገለጠ ጊዜ ሐዋሪያው ቶማስ አብሮዋቸው አልነበረም። ሌሎቹም ደቀ መዛሙርት ‘ጌታን አየነው እኮ!’ ሲሉት ቶማስ ይህ እንዴት ይሆናል ብሎም ተጠራጥሮ ነበር።
“በምስማር የተቸነከሩ የእጆቹን ምልክቶች ካላየሁ፤ምስማሮቹ በነበሩበት ቦታ ጣቴን ካላደረሁ፤ በጎኑም እጄን ካላስገባሁ አላምንም አለ።ከሳምንት በሃላ ደቀ መዛሙርቱ በቤት ውስጥ ሆነው ሳለ ቶማስም ከእነርሱ ጋር ነበር በሮቹም ተቆልፈው ነበር ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆመና ‘ሰላም ለእናንተ ይሁን’ አላቸው። ከዚያም ቶማስን “ጣትህን ወደዚህ አምጣ፤ እጆቼን ተመልከት፤እጅህን ዘርጋ እና በጎኔ አስገባ፤ አትጠራጠር፤እመን አለው። ቶማስም ጌታዬ አምላኬ አለው!’ ዮሐ 20፤21-29
ክርስቶስ ለተጠራጣሪው ቶማስ ጠባሳዎቹን በማሳየት መቶም እንዲነካው በመጋበዝ ከሙታን መነሳቱን አይቶ እንዲያምን አገዘው። በዚህ ክፍል ላይ ቶማስ ክርስቶስ ያለውን ነገር እንዳደረገ ባይነግረንም ‘ጌታዬ አምላኬ’ ብሎ ክርስቶስን እንዳመለከ እናያለን።
2. አምላክ ሰው ለመሆኑ ምስክር ናቸው
ክርስቶስ አዲስ አካልን ለብሶ ሞትን ድል ነስቶ ሲነሳ አንዲት ጠባሳ የሌለበት አካል ቢይዝ በእርግጥ ለእኛም አይምሮ ለመረዳት የበለጠ የተመቸ ይሆን ነበር።በአንፃሩ ደግሞ ሞትን ድል ለመንሳቱ የሰው ልጅን ሃጢአት እና ህመም ለመሽከሙ የህማማቱ ትኩስ ቁስል የእሁድ የፋሲካ ጠባሳ መሆኑ ለተከፈለልንን ትልቅ ዋጋ ምስክር ነው።
የክርስቶስ ጠባሳዎች አምላክ ስጋወደሙን መልበሱን፣ በስቅላት ለመሞቱ እና ሞትን ድል የመንሳቱ ምልክት ናቸው። አምላክም በምድር ላይ ለነበረው ግዜ ለሰውም የከፈለው ዋጋ የዘላለም ማስታወሻ የትንሳሄውም ማረጋገጫ ናቸው።
3. የክርስቶስ ቁስል የእኛ ደስታችን ነው
“ደቀ መዛሙርቱም ጌታን ባዩት ግዜ እጅግ ደስ አላቸው።” ዮሐ 20፤19
ዮሐንስ ሐዋሪያቱ የክርስቶስ እጆች እና ጎኑን ሲያዩት ደሰ እንዳላቸው ይነግረናል። ቁስሎቹም የደስታ ምንጭ ሆነውላቸዋል። ይህ የሚከብድ አባባል ቢሆንም እነዚህ ጠባሳዎች ትላንት ክርስቶስ ለነበረው ሕመም እና ስቃይ ሐዋሪያቱም ለተሰማቸው ሀዘን ባዶነት እና ተስፋ መቁረጥ ልዩ ማስታወሻ ናቸው። የጌታችንን ሐዘን በማሰብ መልሰው ሀዘን አይቀመጡም፤ደረታቸውንም አይደቁም ምክንያቱም እርሱ ጌታቸው አሁን በፊታቸው ሁሉን ድል ነስቶ ቆሟል። ሐዘናቸውንም በደስታ ቀይርዋል።
እኛም ዛሬ ላይ ሆነን ክርስቶስ በመስቀል ላይ ለሃጢያታችን የከፈለውን ዋጋ ስናስብ በሙሉዕ አክብሮት በሙሉዕ ስግደትና አምልኮ አምላካችን ፊት በመቅረብ ነው። የሃጥያታችንን ቅጣት ሁሉ በመስቀሉ ላይ ተከፍሏልና ከአምልኮ እና ምስጋና ባሻገር ልንጨምር የምንችለው ወይም ለሃጢያታችን ብለን የምንከፍለው ቅጣት የለም።
4. በአምላክ የእጅ መዳፍ ተቀርፀናል
“እናት የምታጠባውን ልጆን ልትረሳ ትችላለችን? ለወለደችውስ ልጅ አትራራለትምን? ምናልባት እርሳ ትረሳ ይሆናል እኔ ግን አልረሳሽም።እነሆ በእጄ መዳፍ ቀርጬሻለሁ።” ኢሳ 49:15-16
ልጅ እያለሁ ይህን ክፍል ሳነብ እግዚአብሔር በእጁ መዳፍ ላይ በማይለቅ ብዕር ስሜን እንደፃፈው አስብ ነበር። ኋላ ግን በእጄ መዳፍ ቀርጬሻለሁ ሲል ስሜን ከማስታወስ እጅግ ያለፈ ነገር እንደሆነ ተረድቻለሁ።ኢየሱስ በእጁ መዳፍ ላይ ስለእኔ ሃጢአት የከፈለውን ዋጋ ያዘሉ ቅርፆች ናቸው ለካስ ያሉት? እኔ በዚች ምድር ባላኝ ህይወት ስዝል ስደክም እና ስወድቅ የሚያነሱኝ እጆቹ ለእኔ የሚገባውን ቅጣት የከፈለበትን ደረስኝ የያዙ ናቸው።በአብም ዘንድ ስለእኔ ሲማልድ ለሃጢአቴ ለከፈለው ዋጋ መታያዎች ናቸው።
5. የቆሰለው አዳኛችን ዛሬም በታላቅ ክብሩ በሰማያት አለ፤እኛም አንድ ቀን እናየዋለን
“ከዚያም ተመለከትሁ የብዙ መላዕክትም ድምፅ ሰማሁ ቁጥራቸው ሺህ ግዜ ሺህ እልፍ ግዜ እልፍ ግዜ ነበር፤ እርሱም ከዙፋኑ በሕያዋን ፍጡራን በሽማግሌዎቹም ዙሪያ ከበው ነበር፤በታላቅ ድምፅም እንዲህ ብለው ዘመሩ፤
ለታረደው በግ ሃይል እና ባለፀግነት
ጥበብ እና ብርታት
ክብር እና ሞገስ ምስጋናም
ሊቀበል ይገባዋል።”
ስለእኛ የቆሰለው ኢየሱስ የታረደው በግ ዛሬም በዙፋኑ ላይ በምስጋና ተከብዋል።
“ለወደደን ከሃጢያታችንን በደሙ ነፃ ላወጣን አምላኩን እና አባቱን እንድናገለግል መንግስትና ካህናት ላደረገን ለእርሱ ክብር እና ሃይል ከዘለዖለም እስከ ዘለዖለም ይሁን አሜን
እነሆ አምላካችን ይመጣል
የወጉት እንክዋ ሳይቀሩ
ዐይን ሁሉ ያየዋል።”
ዮሐ ራዕይ 1፡ 5-7
አምላካችን ዳግም ይመጣል! አልያም እኛ ወደ እርሱ እንሄዳለን።በአይናችን ስለእኛ የተወጉትን እጆቹን እግሮቹን እና ጎኑን እናየዋለን!
ማራናታ! አሜን ጌታ ሆይ ቶሎ ና!
